የተቋሙ አመሰራረት ታሪካዊ ዳራ
የአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ልማትና እድገት አስተማማኝነትና ቀጣይነት የሚመዘነው በሰው ኃይል ላይ በሚደረገው ያልተቋረጠ የአቅም ግንባታ ስራ ነው፡፡ ዓለማዊ፣ አህጉራዊ፣ አገራዊ እና አካባቢያዊ ተጨባጭና ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን ጠንቅቆ የሚረዳና በአደገ አስተሳሰብ ለውጡን የሚመራ አመራርና ባለሙያ ለበለጸገ ሀገረ መንግስት ግንባታ ያለው ፋይዳ ብዙ ነው፡፡ አዲስ አበባ ከተማችንም የኢትዮጵያና የአፍሪካ መዲና እንዲሁም የታላላቅ አለም አቀፋዊና አህጉራዊ ተቋማት መቀመጫ እንደ መሆኗ መጠን በከተማዋ የሚሰጡ አገልግሎቶች ሰፊና ውስብስብ በመሆናቸው የአመራሩና የባለሙያው አቅም እና ብቃቱ ይህን ሊሸከም በሚችል አግባብ መገንባት አለበት፡፡ የሰው ኃይል አቅምን ለመገንባት የሚደረጉ ርብርቦች እያደገ ከመጣው የአገልግሎት አሰጣጥና የህብረተሰቡ ፍላጎት ጋር በተጣጣመ መልኩ ተከታታይ፣ ተመጋጋቢና ውጤታማ መሆን እንዳለበት ምሁራን ይናገራሉ፡፡ የአቅም ግንባታ ስራው ተቋማዊ አደረጃጀትን ተከትሎ እና በጥናትና በምርምር ተደግፎ ውጤታማ በሆነ አግባብ መመራት እንዳለበት የአገራችንም ሆነ የአለም ተሞክሮዎችም ያሳያሉ፡፡
ይህን መነሻ በማድረግ በተሻሻለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር ፫፻፷፩/፲፱፻፺፭ አንቀጽ ፳፫/፩ (ረ) እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስፈፃሚና ማዘጋጃ ቤት አገልግሎት አካላት እንደገና ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር ፴፭/፪ሺ፬ በአንቀጽ ፹፬ በተሰጠው ስልጣን መሠረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለያዩ ወቅቶች የሚያደርገውን የተልዕኮ እና የአደራጃጀት ማሻሻያ ለውጥ መሰረት በማድረግ የዛሬው የአዲስ አበባ አመራር አካዳሚ ስራውን ሲሰራ ቆይቷል፡፡
አካዳሚው ቀደም ሲል በደንብ ቁጥር 67/2007 የአዲስ አበባ መለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ በሚል ስያሜ ተጠሪነቱ ለከንቲባ ሆኖ በሥራ አመራር ቦርድ እንዲተዳደር የተቋቋመ ተቋም ነበር፡፡ በኋላም አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የከተማውን አስፈጻሚ አካላት መልሶ የማደራጀት ስራ ሲሰራ ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር በማካሄድ በስልጠና፣ በምርምር፣ በማማከርና በማህበረሰብ አገልግሎት የከተማ አስተዳደሩን አመራርና ባለሙያ አቅም እንዲገነባ በአዋጅ ቁጥር 64/2011 ስልጣንና ተግባር ተሰጥቶት መልሶ እንዲደራጅ ተደርጓል፡፡ በመጨረሻም 6ኛውን አገራዊ ምርጫ ተከትሎ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አስፈጻሚ አካላትን እንደገና ሲያደራጅ ተቋማችን አዲስ አበባ አመራር አካዳሚ የሚል ስያሜ አግኝቶ በቦርድ እንዲተዳደር እና ተጠሪነቱም ለከንቲባ እንዲሆን በአዋጅ ቁጥር 74/2014 የወሰነ ሲሆን በፊት ከነበሩት ስራዎቹ በተጨማሪም የትምህርት ስራን እንዲያከናውን ተግባርና ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡
አካዳሚው ከተቋቋመበት ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን የከተማችን ብቸኛው የመንግስት አመራር ስልጠና ተቋም ሆኖ ከማዕከል እስከ ወረዳ ለሚገኙ አመራሮች እና ባለሙያዎች በጥናትና ምርምር ላይ የተመሰረቱ ስልጠናዎችን፣ የምርምር ስራዎችን፣ የማማከርና የማህበረሰብ አገልግሎቶችን ሲሰጥ የቆየና አሁንም እየሰጠ ያለ ተቋም ነው፡፡ አገልግሎት በሰጠባቸው ዓመታት ውስጥ ከ20 በላይ ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምሮችን በማካሄድ ለሚመለከታቸው ተቋማት እና ለባለድርሻ አካላት ተደራሽ አድርጓል፡፡ ከ 43 ተቋማት ለተወጣጡ ቁጥራቸው 24 ሺ 500 ለሚደርሱ አመራር እና ባለሙያዎች ስልጠና ሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም ለተለያዩ ተቋማትና የህብረተሰብ ክፍሎች የመማከርና የማህበረተሰብ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡
